ማስጠንቀቂያ ለ20/80 እና 40/60 ባለዕጣዎች ተሰጠ

ቁልፍ ያልወሰዱ የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች በቀናት ውስጥ እንዲረከቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

በተለያዩ የግንባታ ሳይቶች ከሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል ግንባታቸው ተጠናቆ ቁልፍ እንዲወሰዱ የተነገራቸው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች ባለመምጣታቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በቀናት ውስጥ ቁልፍ እንዲወስዱ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ቁልፍ ላልተወሰደባቸው ቤቶች የሚያደርገውን ጥበቃ እንደሚያነሳ አስታውቋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚገኙባቸው ፕሮጀክት ሳይቶች በሙሉ የተለጠፈው የኮርፖሬሽኑ ማስጠንቀቂያ፣ የሕንፃና የቤት ቁልፍ ርክክብ ከተጀመረ ብዙ ወራት ቢቆጠሩም ነዋሪው ቤቱን ተረክቦ እያደሰና እየገባ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ በዚህም ምክንያት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶች ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ በመሆናቸው፣ ነዋሪዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስከ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ መጥተው ቁልፍ እንዲረከቡ ያሳስባል፡፡ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ቁልፍ የማይረከቡ ዕድለኞች ቤቶችን በተመለከተም፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊነት እንደማይወስዱ  ተገልጿል፡፡

 

ይህ ዓይነቱ ማስጠንቀቂያ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ባለባቸው እንደ ኮዬ ፈጬ፣ መሪ ሎቄና አያት ለመሳሰሉ 15 ሳይቶች እንደተሰጠ ለሪፖርተር የተናገሩት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውራሪስ ከበደ፣ በእነዚህ ሳይቶች ውስጥ ለነዋሪዎች ርክክብ ደረጃ የደረሱ ከ55 ሺሕ የማያንሱ ቤቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ይሁንና አብዛኛዎቹ ዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሊረከቡ አልቻሉም፡፡ ዳይሬክተሩ ኮዬ ፈጬ ፕሮጀክት አሥርን በምሳሌነት አንስተው፣ በፕሮጀክቱ ለርክክብ የተጠናቀቁ 9,000 ያህል ቤቶች ቢኖሩም መጥተው ማፅዳት እንዲጀመርና ወደ ቀጣይ ደረጃ እንዲሻገሩ ጥሪ ከቀረበላቸው ነዋሪዎች ውስጥ የመጡት 4,000 አይሞሉም ብለዋል፡፡

ዕድለኞች የእነዚህን ቤቶች ቁልፍ እንዲረከቡ ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ እንደ ቀለም መቀባት ያሉ ቀሪ ሥራዎችን በራሳቸው ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ያስረዱት አቶ አውራሪስ፣ ‹‹ያላለቁትንም ቢሆን ተረክበው ማሟላት ያለብንን እያሟላን  እንሰጣቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ቤቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ ያለ ባለቤት ሲቀመጡ ዕቃዎች የሚሰረቁበት አጋጣሚ እንዳለ ገልጸው፣ አሁን ኮርፖሬሽኑ የቀጠራቸው ጥበቃዎች ይኼንን እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ካልመጡ ኮርፖሬሽኑ ጥበቃዎቹን እንደሚያነሳ አስታውቀዋል፡፡

ቁልፍ አልተወሰደባቸውም ተብለው ቅሬታ የቀረበባቸው እነዚህ ቤቶች በ2011 ዓ.ም. በወጣው በ13ኛው ዙር የ20/80 ዕጣ፣ በሁለተኛው ዙር የ40/80 ዕጣ፣ እንዲሁም እንደ የልማት ተነሺነት ባሉ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ለነዋሪዎች የተሰጡ ናቸው፡፡ በተለመደው አሠራር መሠረት ነዋሪዎቹ ቁልፍ በመረከብ በየብሎኩ በኮሚቴ በመደራጀት ጥበቃ ማቆምን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ በቤቶቻቸው ግንባታ ላይ ጉድለት ተፈጥሮም ከሆነ ቅሬታ እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡

ይሁንና እነዚህን ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ ቢጠየቅም ብዙዎቹ እንደ ውኃ፣ መብራትና መንገድ ያሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች አልተሟሉላቸውም፡፡

በኮዬ ፈጬ ፕሮጀክት አሥር የቁልፍ ርክክብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አይጠገብ ውዴ እንደሚያስረዱት፣ በዚህ ፕሮጀክት ሥር ያሉ ቤቶች የመፀዳጃ ቤት መፋሰሻ ስላልተሠራ ነዋሪዎች ቁልፉን ቢረከቡም ገብተው መኖር አይችሉም፡፡ ይሁንና እንዲህ ዓይነት የመሠረተ ልማት ጉዳዮችን የሚመለከተው እንደ ውኃና ፍሳሽ ያሉ ተቋማትን እንጂ፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ነዋሪዎች ቁልፍ ላለመረከባቸው ይኼ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አይጠገብ፣ ከባንክ ጋር የክፍያ ፕሮሰስ ያልጨረሱ እንዳሉም  ተናግረዋል፡፡ ሰብሳቢው፣ ‹‹ይሁንና በተለይ አርሶ አደር ነዋሪዎች ቁልፍ እንዲረከቡ ቢጠየቁም፣ ከተረከብን እንሰረቃለን በማለት ኃላፊነት ላለመውሰድ መንግሥት መብራትና ውኃን አጠናቆ ያስረክበን ይላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውራሪስ በበኩላቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀው፣ ‹‹ኃላፊነቱ የጋራ ነው መሆን ያለበት፣ እኛ ብቻ ቤቶቹን እየጠበቅን መቆየት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1 ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top