በመሬትና ይዞታ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕግድ በቅርቡ ይነሳል ተባለ news

በመሬትና ይዞታ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕግድ በቅርቡ ይነሳል ተባለ

.
471 ሺሕ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች እንዲመክኑ መደረጉ ተነግሯል
88 የመሬት ጉዳይ ሠራተኞች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዶ የቆየውን የመሬትና ይዞታ ነክ አገልግሎቶች በቅርቡ እንደሚያስጀምር አስታወቀ፡፡
.
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማት ቅንጅትና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም ለ11 ክፍላተ ከተሞች አስተላልፎት በነበረው ሰርኩላር፣ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡
.
የከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ለግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ፣ በተለይም ከግንባታ ፈቃድ ጋር ተያይዞ ታግደው የቆዩ አገልግሎቶች እግድ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡ ሆኖም ከመሬትና ከይዞታ ጋር የተገናኙ አገልግሎቶች ዕግድ ባለበት ቀጥሏል፡፡
.
የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል አሊዩ እንዳስታወቁት፣ ለሌብነት ተጋላጭ የሆኑ መሬት ነክ አገልግሎቶች በጊዜያዊነት እንደታገዱ ቆይተዋል፡፡
.
የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት የጀመራቸው አገልግሎቶች ከግንባታ ፈቃድ ጋር የተገናኙትን እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጀማል፣ ከመሬትና ይዞታ ጋር የተገናኙ አገልግሎቶች፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአስተባባሪ ኮሚቴ ታይተው እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል፡፡ አገልግሎቱ በየትኛው ቀን ይጀመራል የሚለውን ያልጠቀሱት ኃላፊው፣ ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር አስምረውበታል፡፡
ይህ ብቻም ሳይሆን የከተማ አስተዳደሩ ለሊዝ ጨረታ የሚሆኑ ቦታዎችን ካቀረበ ከሦስት ዓመታት በላይ እንደሆነው ያስረዱት አቶ ጀማል፣ በተያዘው ዓመት ግን የከተማ አስተዳደሩ በሊዝ ጨረታ የሚያቀርበው መሬት ይኖራል ብለዋል፡፡
.
በተያያዘም አስተደዳሩ በጥቅምት ወር ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ሕገወጥ ተግባራትን ፈጽመዋል የተባሉ አካላትን ካሳወቀበት ጊዜ አንስቶ የተወረሩ መሬቶችን የመለየት፣ መሬቶቹ በማን ነው የተወረሩት፣ በወረራ ውስጥ እጃቸው ያለበት የመንግሥት አመራሮችና ፈጻሚዎች፣ እንዲሁም መሬቱን ያላግባብ ለመጠቀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች እነ ማን ናቸው? የሚለውን ለመለየት የሚያስችል በከተማ ደረጃ የተዋቀረ የአስተባባሪ ኮሚቴ በበላይነት የሚመራው ግብረ ኃይል በየክፍላተ ከተሞቹ ተቋቁሞ፣ የመሬት ኦዲት ሲያደርግ የቆየበትን ሪፖርት ሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡
.
በሪፖርቱ ከዚህ ቀደም ከተጠቀሱትና አስተዳደሩ ኦዲት ካከናወነባቸው ቦታዎች 671 የሚሆኑት ተለይተው ዕርምጃ እንደተወደባቸው ተገልጿል፡፡ ይህም ማለት የባለቤትነት መብታቸውን የሚያስነጥቅ የካርታ ማምከን መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
.
ዕርምጃ የተወሰደባቸው መሬቶች ስፋታቸው 260,106 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ መሬቶቹ ግንባታቸው በተለያየ ደረጃ ላይ የደረሱ ቢሆኑም አስተዳደሩ ግንባታዎቹ እንዲፈርሱ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ መሬቶቹ በቀጥታ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን፣ በሒደቱ የአርሶ አደር ይዞታ ሆነው የተገኙት ለአርሶ አደሮች፣ የመንግሥት የነበሩት ደግሞ ወደ መንግሥት እንዲመለሱ ተደርገዋል ተብሏል፡፡ ለሚ ኩራ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ክፍላተ ከተሞች ወረራዎቹ በስፋት የተፈጸሙባቸው መሆናቸውን፣ እንደ ሌሎቹ ክፍላተ ከተሞች ባይሆንም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ወረራው መከናወኑ ተገልጿል፡፡
.
በሕገወጥ መንገድ የተያዘውንና የተወረረውን መሬት ከማስመለስ ባሻገር በሕገወጥ ተግባሩ የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ መሆን ስላለባቸው፣ አስተዳደሩ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደወሰደ ተገልጿል፡፡ የፖለቲካ ዕርምጃ ከተወሰዱት መሀል የሚጠቀስ መሆኑን፣ በዚህ ሒደት የተሳተፉ የመሬት ነክ ጉዳይ አመራሮች ከፖለቲካ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ተብራርቷል፡፡
.
ከአመራሮች በተጨማሪ ለድርጊቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሲያመቻቹ የነበሩ ፈጻሚ አካላት ላይ ከክፍላተ ከተማ እስከ ወረዳ የሚገኙ 88 የሚደርሱ ፈጻሚዎች ከሥራ የማገድ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ሕግ መሠረት ለሕግ ቀርበው አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ሒደቱ እንደቀጠለ አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡
.
ለሕግ የቀረቡት አካላት ዝርዝር መረጃ የሕግ ጉዳዩን የሚከታተለው አካል በራሱ መንገድ የሚገልጽ እንደሆነ፣ በዚህ ወቅት ለሕግ የሚቀርቡ አካላት መኖራቸውን መግለጽ ብቻ በቂ እንደሆነ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከኅዳር 1 እስከ ታኅሳስ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ብቻ በተለየ ማጣራት 1,088 ቦታዎች ያላግባብ ተወረውና ግንባታ ተፈጽሞባቸው በመገኘታቸው የቦታዎቹ ባለቤትነት ተቀልብሶ ወደ መንግሥት ለመመለስ እንደተቻለ ተገልጿል፡፡
.
አቶ ጀማል እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የነበረው የይዞታ ካርታ ኅትመት የሚሠራው በማዕከል ቢሆንም፣ የመሬት ይዞታ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሥርጭቱ የሚከናወነው በክፍላተ ከተሞች ነው፡፡ በክፍላተ ከተሞቹ የሚሠራጩት ካርታዎች ለተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች ተጋላጭ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት  ያላግባብ በየክፍላተ ከተሞች ተሠራጭተው የሚገኙ ካርታዎች ለሕገወጥ ወረራ ተጋላጭ እንዳይሆኑ፣ 472 ሺሕ ካርታዎች ተለይተው እንደተሰበሰቡና ምናልባትም ካርታዎቹ በግለሰቦች እጅ ላይ የደረሱበት አጋጣሚ ይኖራል በሚል ጥርጣሬ ካርታዎቹ መምከናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላም አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ የተለየ ካርታ አዘጋጅቶ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አቶ ጀማል አክለው ተናግረዋል፡፡
.
ከዚህ በኋላ መሬትን መሸጥም ሆነ መለወጥ የሚቀጥል ጉዳይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ሆኖም ሰዎች መሬት በሽያጭ ሲተላለፍላቸው መጠንቀቅ ያለባቸው ጉዳይ ቢኖር በመንደር ውል የሚደረግ እንቅስቃሴ ዋስትና እንደማይሆን ነው፡፡ መንግሥት ዕርምጃ ከወሰደባቸው አብዛኞቹ መሬቶች በመንደር ውል የተፈጸሙ መሆናቸው መሬት በግዥ ወደ ራሱ ማስተላለፍ ያሰበ አካል በመጀመርያ መሬት ልማትና አስተዳደር በመምጣት መሬቱ ሕጋዊነቱንና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳለውና የፕላን ፎርማቱ ምንድነው የሚያሳየው የሚሉትን ሕጋዊ ጉዳዮች ካጣራ በኋላ በውልና ማስረጃ ብቻ እንዲፈጽም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
Ethiopian Reporter
https://m.youtube.com/channel/UCpasn6BWeJnYIRAr1nqr5dw

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top