የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ40/60 ቤቶች አቤቱ ውድቅ ተደረገ

መመርያን በቃለ ጉባዔ የሻረው ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ40/60 ቤቶች ላይ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

.
የቀድሞ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥን በሚመለከት ያወጣውን መመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 16 ድንጋጌን፣ በቃለ ጉባዔ በመሻር፣ መቶ በመቶ (100 ፐርሰንት) ክፍያ የፈጸሙ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች መብትን ለመጣስ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን (የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ) ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ የተደረገው፣ በሥር ፍርድ ቤት (የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት) ውሳኔ የተሰጠበትን፣ የፍርድ አፈጻጸም ተከፍቶበት የነበረንና ዕጣ ከመውጣቱ በፊት በመመርያው መሠረት መቶ በመቶ ክፍያ መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ መብታቸውን በሕግ ለማስጠበቅ ክስ መሥርተው ከነበሩ ከ738 በላይ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ጋር በተያያዘ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀድሞ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል (ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል)፣ በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ መውጣቱ ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስካሁን ድረስ (ታኅሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ) ለዕድለኞቹ ያልተላለፉ ቢሆንም፣ በተለይ የተወሰኑ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ከ660 በላይ ቤቶች ይሆናሉ) የሕግ ጥያቄ ስለተነሳባቸው ዕግድ ተጥሎባቸው ነበር፡፡
በተጠቀሱት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ዕግድ ሊጣል የቻለው፣ በምዝገባ ወቅት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አውጥቶት በነበረው፣ የዕጣ አወጣጥ መመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 16 ድንጋጌ መሠረት፣ በምዝገባ ወቅት መክፈል ያለባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት ክፍያ (40/60 ክፍያ) መቶ በመቶ ከከፈሉ፣ የዕጣ ውድድሩ የሚደረገው ሙሉ ክፍያ በፈጸሙ ተመዝጋቢዎች መካከል እንደሆነ በመመርያው ተደንግጎ ቢገኝም፣ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣው እንዲወጣ የተደረገው ሁሉንም 20 እና 40 ፐርሰንት ተመዝጋቢዎችን ያካተተ በመሆኑ ነበር፡፡
በወቅቱ የዕጣ አወጣጡ መመርያውን የጣሰና ክፍያ ሲፈጽሙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የገቡትን ኮንትራት (ሕግ) የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ፣ እነ አቶ አድማሱ ካሳ (98 ሰዎች) ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ወስደውት ነበር፡፡ መረጃው የደረሳቸው ሌሎች የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች የሕግ ክርክሩን በመቀላቀል ባደረጉት ክርክር የሥር ፍርድ ቤት ከላይ የተጠቀሱትን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲታገዱ በማድረግ ክርክሩ ቀጥሏል፡፡ ክፍያ የፈጸሙት ከሳሾች ከከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡
ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሙሉ በሙሉ ክፍያ የፈጸሙትን መብት በማለፍ፣ ዕጣው ለሁሉም ተመዝጋቢዎች እንዲወጣ ያደረገው፣ በሚኒስቴሩ የወጣውን መመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 16 ድንጋጌን በቃለ ጉባዔ በመሻር ነበር፡፡ ነገር ግን ክርክሩን ሲሰማ የከረመው የሥር ፍርድ ቤት፣ ከሳሾች ያቀረቡት ክስ ተገቢ መሆኑ በማረጋገጥ፣ በቁጥራቸው ልክ የታገደው የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው ፍርድ ሰጥቶ አፈጻጸም ከፍተው ነበር፡፡
የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ ቢተገበር ከፍተኛና ሊመለስ የማይችል ጉዳት ሊያደርስበት እንደሚችል በመግለጽ፣ አፈጻጸሙ እንዲታገድለት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡
የይግባኝ አቤቱታውን የመረመረው ይግባኝ ሰሚው ችሎቱ፣ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ‹‹መመርያውን በቃለ ጉባዔ የሻረው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን በሰጠው ትዕዛዝ ላይ አብራርቷል፡፡ እንደመረመረውም፣ ይግባኝ ባዩ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ‹‹መመርያው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የዜጎች የእኩልነት መብት የሚጥስ ነው›› በማለት በሥር ፍርድ ቤት መከራከሩን አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ እንዳለው (እንደ ተከራከረው) መመርያው ጉድለት እንዳለበት ቢረጋገጥ እንኳን፣ ሊሻር የሚችለው ተገቢውን ሥርዓት ተከትሎ እንጂ በቃለ ጉባዔ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም መመርያውን ያወጣው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም መመርያ የማውጣት ሥልጣን እንዳልነበረውና ሥልጣን የሌለው አካል ያወጣው መመርያ ደግሞ ‹‹ተጥሷል›› ሊባል እንደማይችልም አብራርቷል፡፡ ሌላው ኮርፖሬሽኑ በይግባኝ አቤቱታው ያቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ፣ በሥር ፍርድ ቤት ያልተጠቀሰና ያልተነሳ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ፣ በአፈጻጸሙ ላይ ጥሎት የነበረው ዕግድ መነሳቱንና የሥር ፍርድ ቤት ሰጥቶት በነበረው ውሳኔ መሠረት አፈጻጸሙ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን አቤቱታን ውድቅ አድርጎታል፡፡    
ምንጭ:-Reporter

Https://m.youtube.com/channel/UCpasn6BWeJnYIRAr1nqr5dw

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top