በአዲስ አበባ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደው የቤት ግብር ማሻሻያ ምን ዝርዝር ይዟል?

በአዲስ አበባ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደው የቤት ግብር ማሻሻያ ምን ዝርዝር ይዟል?

በአማኑኤል ይልቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው አዲስ የቤት ግብር ማሻሻያ መሰረት የቤት ባለቤቶች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንዲፈጽሙ፤ በሶስት መቶ ሺህ ገደማ ቤቶች ላይ የግብር ግመታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ። ቤቶቹን የመለየት እና ግብር የመገመት ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የቤት ግብር የማይከፈልባቸው ቤቶች ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የእነዚህ ቤቶች ባለቤቶች ሊከፍሉ የሚገባውን የቤት ግብር የመለየት ስራ እያከናወነ ያለው፤ የከተማዋ የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ነው። በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የመሬት ይዞታዎችን መረጃ በዲጂታል እና በወረቀት የመያዝ ኃላፊነት በአዋጅ የተጣለበት ኤጀንሲው፤ የሰበሰባቸውን መረጃዎች ጥቅም ላይ የማዋል ስልጣንም ተሰጥቶታል።

በዚህም መሰረት ኤጀንሲው እስካሁን ድረስ 147 ሺህ ይዞታዎች ላይ የማረጋገጥ ስራ አከናውኖ፤ መረጃቸውን በዲጂታል መንገድ መያዙን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ዴሲሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኤጀንሲው በራሱ ካደረጋቸው ማረጋገጫዎች ባሻገር “የባለቤትነት መብት የተመዘገበላቸው” የሪል ስቴት እና ኮንዶሚኒየም ቤቶችን መረጃ መያዙን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በተቋሙ የመረጃ ቋት ውስጥ ያሉ የቤት ይዞታዎችን ቁጥር 363 ሺህ እንደሚያደርሰው አመልክተዋል።

ይኸው የከተማይቱ መስሪያ ቤት በመረጃ ቋቱ ውስጥ ያሉ ቤቶችን ስፋት እና ያረፉበትን መሬት ደረጃን መሰረት በማድረግ፤ ለእያንዳንዱ ይዞታ የቤት ግብር ስሌት ግመታ እያከናወነ መሆኑን አቶ ግፋወሰን አስታውቀዋል። ኤጀንሲው ይህንን ስራ እያከናወነ ያለው፤ የአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ ቢሮ ከዚህ ቀደም አነስተኛ የሆነ ገንዘብ ሲከፈልበት በነበረው የቤት ግብር ላይ የማሻሻያ ተመን ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የተደረገው ይህ ማሻሻያ መሰረት ያደረገው፤ ከ47 ዓመታት በፊት የወጣውን የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር አዋጅን ነው። በከተሞች የሚገኙ የቤት ባለቤቶች የንብረት ታክስ (property tax) እንዲከፍሉ የሚያስገድደው የ1968ቱ አዋጅ፤  የግብር ተመን የሚሰራው ቤቱ በምን ያህል ዋጋ ሊከራይ ይችላል በሚል ግምት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ደንግጎ ነበር። በዚህ ግምት መሰረት፤ የመኖሪያ ቤቶች ባለቤቶች ከሚያከራዩት ዓመታዊ ዋጋ ከ1.5 እስከ 4.5 በመቶ ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ይህንን ግብር ለመተመን ጥቅም ላይ የሚውለው የቤት ኪራይ ግምት በየጊዜው መከለስ ያለበት ቢሆንም፤ ከ1988 ዓ.ም በኋላ ክለሳ አለመከናወኑን በአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ የንብረት ታክስ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አስማማው ሙሉጌታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉት ቤቶች የሚሰበሰበው ግብር፤ “እዚህ ግባ የሚባል” አለመሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የቤት ግብር ከሚከፍሉ 183 ሺህ ገደማ መኖሪያ ቤቶች የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ፤ 47.7 ሚሊዮን ብር መሆኑን ከከተማይቱ ፋይናንስ ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ግብር ከሚከፈልባቸው ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ 12 በመቶው የሚከፍሉት “ከአስር ብር በታች” መሆኑን የሚገልጹት አቶ አስማማው፤ 46 በመቶው ደግሞ “ከመቶ ብር በታች” መሆኑን በአጽንኦት ጠቅሰዋል። 2,500 ያህል ቤቶች ከአንድ ብር በታች እንደሚከፍሉ በተጨማሪነት ያነሱት አስተባባሪው፤ “ለዓመታዊ ግብር ከአንድ ብር በታች ማለት በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው። አሁን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ምክንያታዊም አይደለም” ሲሉ አሁን የተደረገውን ማሻሻያው አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።

የፌደራል መንግስት የንብረት ታክስ (property tax) አዋጅ ገና እያዘጋጀ ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን እስከዚያው ድረስ በቀድሞው አዋጅ ላይ ተመስርቶ ከቤት ግብር የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥናት ማድረጉን አስተባባሪው ገልጸዋል። በዚህ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ቤቶች በቦታ ደረጃቸው፣ በተገነቡበት ቁስ እና በአገልግሎት አይነታቸው ተከፋፍለው፤ አዲስ ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ እንደተተመነላቸው አቶ አስማማው አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ ባለፈው ሚያዝያ ወር ባወጣው “የጥናት ውጤት ውሳኔ” መሰረት፤ ቤቶች  ያረፉባቸውን ቦታዎች ታሳቢ በማድረግ በአራት የተለያዩ ደረጃዎች ይከፋፈላሉ። “ደረጃ አንድ” ላይ የሚመደቡ ቦታዎች በጥናቱ ከፍ ያለ የኪራይ ዋጋ ተመን የተገመተላቸው ሲሆን፤ ይህም ታሳቢ ያደረገው ቦታዎቹ ከዋና መስመር ያላቸውን ርቀት እና የተሟላላቸውን መሰረተ ልማት ነው። በቀጣዮቹ ደረጃዎች የተካተቱ ቤቶችም፤ ተመሳሳይ መስፈርትን በመጠቀም የዋጋ ተመን ግምት ዝርዝር ወጥቶላቸዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ ሶስት መስሪያ ቤቶች የተሰራጨው ይኸው ጥናት ከግምት ውስጥ ያስገባው፤ የቤቶቹን የአገልግሎት አይነት ነው። ለመስሪያ ቤት የሚያገለግሉ ቤቶች የተተመነላቸው የኪራይ ግምት፤ ለመኖሪያ ቤት ከሚውሉት ከፍ ያለ ዋጋ በጥናቱ ተሰጥቷቸዋል። ቤቶች በተገነቡበት የቁስ አይነትም የኪራይ ተመን ልዩነት ተቀምጦላቸዋል። በብሎኬት የተሰሩ ቪላዎች፣ አፓርታማዎች እና ህንጻዎች፤ በጥናቱ ከፍ ያለ የዋጋ ተመን ያገኙ ሲሆን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ደግሞ መለስተኛ ትመና ወጥቶላቸዋል። ከእንጨት እና ከጭቃ የተሰሩ ቤቶች ደግሞ ዝቅተኛ የዋጋ ግምት አግኝተዋል።

በዚህ ትመና መሰረት ዝቅተኛ ዋጋ የተተመነው በ“ደረጃ ሶስት እና አራት” በሚገኙ ቦታዎች ላይ ከእንጨት እና ጭቃ ለተሰራ መኖሪያ ቤት ሲሆን፤ የዚህ አይነቱ ቤት አንድ ካሬ የኪራይ ግምት 148 ብር ተተምኗል። በደረጃ አንድ ላይ የሚገኙ ቦታዎች ላይ ተሰርተው ለመስሪያ ቤትነት የሚያገለግሉ ቪላ፣ አፓርታማ እና ተመሳሳይ ህንጻዎች ደግሞ፤ ከፍተኛ የሆነውን የአንድ ካሬ የኪራይ ዋጋ 632 ብር ትመና ተሰርቶላቸዋል።

የከተማዋ ፋይናንስ ቢሮ ባሰራጨው “የጥናት ውጤት ውሳኔ” መሰረት የቤቶቹ ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ በዓመት ተሰልቶ፤ የቤት ባለቤቶች የዓመታዊውን ዋጋ ከአንድ እስከ 4.5 በመቶ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ውሳኔ ላይ በ“ደረጃ አንድ” ላይ የሚገኝ ባለ 54 ካሬ ሜትር ለመኖሪያነት የሚያገለግል ኮንዶሚኒየም፤ በዓመት 7,103 ብር የቤት ግብር እንደሚከፈልበት በማሳያነት ተጠቅሷል። በጥናቱ መሰረት የቤት ባለቤቶች መክፈል የሚጠበቅባቸው ተመን ቢዘጋጅም፤ በዚህ ዓመት ግን ሙሉውን ክፍያ መክፈል እንደማይጠበቅባቸው የፋይናንስ ቢሮው ባሰራጨው የውሳኔ ደብዳቤ ላይ አስታውቋል።

ሁሉም የመኖሪያ ቤት ባለቤቶች በአዲሱ ተመን መክፈል ከሚጠበቅባቸው ዓመታዊ ግብር ውስጥ፤ በዚህ ዓመት የሚከፍሉት ግማሹን ብቻ መሆኑን የቢሮው ደብዳቤ አመልክቷል። ለመስሪያ ቤትነት የሚውሉ ቤቶች ባለቤቶች ደግሞ በዚህ ዓመት መክፈል የሚጠበቅባቸው ከአዲሱ ተመን 75 በመቶውን እንደሆነ በፋይናንስ ቢሮ ደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል። ይህ የተደረገው በአዲሱ ተመን ሊመጣ የሚችለውን “የክፍያ ጫና ለማቅለል” እንደሆነ ቢሮው በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት ግብርን በተመለከተ ያመጣው አዲስ ጉዳይ፤ የግብር ተመን ማሻሻያ ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም ይህንን ግብር የማይከፍሉ የከተማዋ ቤቶችን በዚህ ስርዓት ውስጥ የማካተት ውሳኔም መተላለፉን የንብረት ታክስ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪው አቶ አስማማው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እስካሁን ወደ ስርዓቱ አልገቡም ተብለው ከተለዩት ውስጥ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንደሚገኙበትም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ 300 ሺህ ገደማ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን መገንባቱን ያስታወሱት አስተባባሪው፤ ሆኖም እነዚህ መኖሪያዎች የቤት ግብር ሳይከፈልባቸው “ተረስተው ቆይተዋል” ብለዋል። በሪል ስቴቶች የሚገነቡ ቤቶችም በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ አይነቱ ግብር ውጪ ሆነው መቆየታቸውንም አስረድተዋል። በከተማዋ ውስጥ የቤት ግብር የሚከፍሉት አብዛኛዎቹ “ነባር ይዞታዎች” መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አስማማው፤ በአዲሱ ጥናት ግን ኮንዶሚኒየም እና የሪል ስቴቶችን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ቤቶች የቤት ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ወር ያስተላለፈውን ይህንን ውሳኔ ተከትሎ፤ ከዚህ ቀደም የቤት ግብር ይከፍሉ የነበሩ የቤት ባለቤቶች በአዲሱ ተመን መሰረት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ እየተደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳስን እና አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ወንድም አገኘሁ ካፋይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ግብር የማይከፍሉ የነበሩ ቤቶችን በተመለከተ ደግሞ፤ የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ የአዲሱ ተመን ግመታ እንደደረሰው ወደ ክፍያ ማስፈጸም እንደሚገባ አስረድተዋል። አዲሱን ክፍያ በተመለከተም ለእያንዳንዱ የቤት ባለቤት፤ የታክስ ማስታወቅ ስራ እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ምንጭ ፡- (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top