መንግሥት የመኖሪያ ቤቶችን እየገነባ የቤት ባለቤት ማድረግ አይችልም ተባለ!

መንግስት ኮንዶሚኒየም መሥራት አቆመ!**

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለማቃለል አስተዳደሩ በአማራጭነት ባቀረባቸው የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የመኖሪያ ቤቶችን መገንባት እንደሚቻልና ኅብረተሰቡም በዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አስተላለፉ፡፡

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት ሰሞኑን ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የገነባቸውን አምስት ሺሕ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ባስተላለፈበት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ እንደ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ገለጻ፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤቶችን እየገነባ የቤት ባለቤት ማድረግ የማይችል በመሆኑ አስተዳደሩ አዲስ በቀረጻቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ መሆን የሚቻልበት ዕድል ማመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡ በከተማዋ ነዋሪዎች በዋነኛነት የሚነሳው የመኖሪያ ቤት ችግር መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ አስተዳደሩም ይህንን ጉዳይ ከሁሉም በላይ በአንገብጋቢነት እንደሚመለከተው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የቤት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የአማራጮች እየተተገበሩ መሆኑን በማስታወስ የከተማው ነዋሪም እነዚህን አማራጮች መጠቀም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ የተቀየሱት አማራጮችን በመጠቀም የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም አሁንም የመኖሪያ ቤት አቅርባትና ፍላጎቱ ግን ሊጣጣም አልቻለም፡፡ በመሆኑም ይህንን ለማጣጣምና የመኖሪያ ቤት አቅርቦቱን ለመጨመር በርካታ የቤት አቅርቦት ፕሮግራሞች በመቅረጽና አስፈላጊው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት አብሮ የማልማት እንቅሰቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ አቅም ላላቸው የከተማው ነዋሪዎች፣ ለባለሀብቶች፣ ለግል አልሚዎችና ሌሎችም በዚህ ሥራ መሳተፍ የሚችሉትን ሁሉ በማበረታታት ላይ የሚገኙ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በእነዚህ የቤት ግንባታ አማራጮች ለመሳተፍ የሚፈልጉ በሩ ክፍት ስለመሆኑ በመግለጽም አስተዳደሩ በአማራጭነት ባቀረባቸው የቤት ግንባታ አሠራሮች ኅብረተሰቡ ተሳታፊ ይሆን ዘንድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አስተዳደሩ በአማራጭነት ካቀረባቸው የቤት ማልሚያ ፕሮግራም ውስጥ አንዱ በፓርትነርሺፕ ወይም በአጋርነት አብሮ መሥራት በቀዳሚነት ጠቅሰዋል፡፡ ሁለተኛ በሪልስቴት መሬት ሳይሸጥ ዓላማው ሳይቀር በዕለቱ አምስት ሺሕ ቤቶችን እንዳስተላለፈው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተሰጠውን መሬት አልምቶ ለተፈለገው ዓላማ ማዋል መቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተረከቡት መሬት ዓላማው ሳይቀር ለተፈለገው ዓላማ መዋል የሚችል ከሆነ አስተዳደሩ የሚያበረታታ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በአማራጭነት ሊጠቀምበት ይችላል ብለው ሦስተኛ አማራጭ ብለው የገለጹት በማኅበር ተደራጅቶ ቤት መሥራትን ነው፡፡ አራተኛው አማራጭ ደግሞ ከሦስቱ አማራጮች ለየት ባለ መንገድ የሚተገበር ነው፡፡ ይህም ቤት የሚፈልጉ መሬት ያላቸው ገንዘብ ግን የሌላቸው ነዋሪዎች ገንዘብ ካለው አልሚ ጋር በአጋርነት አብረው ማልማት የሚችሉበት ዕድል የተመቻቸ መሆኑ ነው፡፡ አምስተኛ አማራጭ ደግሞ መንግሥት ራሱ እንዲገነባ የሚያቀርበው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ አማራጮች የከተማዋን ዲዛይን በጠበቀ መልኩ የሚገነቡ እስከሆነ ድረስ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያደርግባቸው አዳዲስ አሠራር ስለመሆናቸው ከገለጻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹በየትም አገር የቤት አቅርባት እየጨመረ እንዲሄድ ይደረጋል እንጂ መንግሥት እየገነባ ሁሉንም ነዋሪ የቤት ባለቤት ማድረግ አይችልም፣ በየትኛውም ዓለም አልተደረገም፤›› ያሉት ከንቲባዋ ነገር ግን አዲስ አበባ የቤት አቅርባትን የሚያስችሉ አቅሞቻችንን ማቀናጀት በጋራ ማልማት የሚቻል ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

አሁንም አስተዳዳሩ ይህንን ሥራ ለማጠናከር እየሠራ ሲሆን በዕለቱ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን አምስት ሺሕ ቤቶች ሠርቶ በማስረከቡ በከተማችን በዚህን ያህል ቁጥር የቤት አቅርቦት መጨመር ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሰንሻይን ይህንን ያህል ገንብቶ ቤቶቹን ማስተላለፍ የቻለው መሬቱ ስላልተለወጠ ለተፈለው ዓላማ ስለዋለ መሆኑና ይህም 3.8 ሔክታር መሬት በነፃ አስተዳደሩ የቀረበ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ እንዲህ በትብብር ከተሠራ ውጤታማ መሆን ይቻላልም ማለትም አሁንም ወደፊትትም ቤት ለማልማት አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው በትክክል ማቅረብና መተግበር ለሚችሉ አስተዳደሩ በነፃ መሬት ባያቀርብም በበርካታ ማበረታቻዎችን የሚሰጡና የሚደግፉ መሆናቸውም አስታውቀዋል፡፡ ከንቲባዋ እነዚህ አማራጮች ሌላ ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው ቤት መገንባት የሚችሉ ከሆነ ይህንን ለማበረታታት ቦታ የሚያቀርቡ እንደሆነም በሰሞኑ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ አምስት ሺሕ ቤቶችን ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ወ/ሮ አዳነች ኩባንያዎች ለሠራተኞች ቤት መገንባት የሚፈልጉ ከሆነ ይበረታታሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወሰደውን ዕርምጃ በምሳሌነት በመጥቀስ በከተማ ውስጥ በርካታ ትልልቅ ኩባንያዎች ስላሉ ለሠራተኞቻቸው ቤት በመገንባት የቤት አቅርባትን ችግር ለማቃለል ለሚያደርጉት ጥረት አስተዳደሩ መሬት የሚያቀርብ በመሆኑ ኩባንያዎች ይህንንም የቤት ማልሚያ መንገድ በመጠቀም መገንባት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ በአማራጭነት ካቀረባቸው አሠራሮች ውስጥ በተለይ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ለማልማት በተቀረጸው ፕሮግራም 70 የሚሆኑ አልሚዎች ከአስተዳደሩ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ቀሪዎቹም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲህ ላሉ የቤት ልማቶች አስተዳደሩ 1,500 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱም መገለጹ ይታወሳል፡፡

አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ቁጥር ከ600 ሺሕ በላይ ደርሰዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ በመንግሥት የተገነቡ ቤቶች 316 ሺሕ ሲሆኑ በዚህ የግንባታ ሒደት የቤት ፍላጎትን መሙላት እንደማይችልም በመታሰቡ አስተዳደሩ በአማራጭነት በቀረቡ የቤት ማልሚያ ፕሮግራሞች እየተሳተፉ ያሉ አልሚዎች የቤት ችግርን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎም ታምኖበታል፡፡

ከዚሁ አንፃር በከተማዋ እየተካሄደ ያለውን የቤቶች ልማት በተመለከተ በ2016 በሙሉ በጀት ዓመቱ ግንባታቸውን ለማስጀመር ከታቀዱት 120 ሺሕ ቤቶች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 99113 ቤቶች ማልማት መቻሉን ከንቲባዋ በቅርቡ የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህም ሌላ በበጀት ዓመቱ 111 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የአጋርነት ውልና የመሬት ዝግጅት እየተከናወኑ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ባሉ በአጋርነት ቤት በማልማት ሥራዎች በሪል ስቴት ኩባንያዎችና በግለሰብ አልሚዎች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ አሥር ሺሕ ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በግለሰብና በሪል ስቴት ኩባንያዎች ከተገነቡት አሥር ሺሕ ቤቶች ሌላ በመንግሥት በጀት 4,200 በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በኩል ደግሞ 5023 ቤቶች በአጠቃላይ 19,223 ቤቶች ስለመገንባታቸውም ጠቅሰዋል፡፡

 

ሪፖርተር ጋዜጣ

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top