ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለማቋቋም አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ታወቀ

ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለማቋቋም አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ታወቀ

፦መንግሥት 25 በመቶ የግል ኢንቨስተሮች ደግሞ 75 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል

የኢትዮጵያ ‹‹የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ›› ለማቋቋም አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ የመነሻ ካፒታል ያስፈልጋል ተባለ፡፡

በ2016 ዓ.ም. ወደ ሥራ የሚገባው የሙዓለ ንዋይ ገበያው ትርፍ ለማስመዝገብ ከሦስት እስከ አራት ዓመታት እንደሚፈጅበት፣ በጥናት መታወቁን የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

በሙዓለ ንዋይ ገበያው ውስጥ መንግሥት 25 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው፣ ይህም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በኩል 250 ሚሊዮን ብር ገደማ ያወጣል ተብሏል፡፡ የተቀረው 75 በመቶ ወይም 750 ሚሊዮን ብር ገደማ ደግሞ ለግል ኢንቨስተሮች ከሚሸጥ አክሲዮን እንደሚሰበሰብ ተገልጿል፡፡ ለግል ኢንቨስተሮች አክሲዮን የመሸጥ ሥራ ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሯል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አንድ ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ትንሽ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ መነሻ ካፒታሉን ከዚያ በላይ ከፍ ማድረግ፣ ትርፍ የማስገኛ ጊዜውን ስለሚያረዝም ጉዳት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የሙዓለ ንዋይ ገበያው ሥራ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከስድስት ወራት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልጉ በርካታ ሕጎችን እያዘጋጀ ነው፡፡ ሕጎቹ ከፀደቁ በኋላ ማንኛውም ሰው አክሲዮን ሸጦ ድርጅት ለማቋቋም ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

የሙዓለ ንዋይ ገበያው በሚቀጥለው ዓመት በአንድ ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ወደ ሥራ እስኪገባ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማስተባበርና ከግል ኢንቨስተሮች የሚሰበሰበውን አክሲዮን የመሸጥ ሥራ ያከናውናል ተብሏል፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ማቋቋሚያ ሒደት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥና የገንዘብ ሚኒስትሩ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ትናንት በሸራተን አዲስ ከባንክና ኢንሹራንስ ኃላፊዎች ጋር ዝግ ስብሰባ አድርገዋል፡፡

‹‹ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት ለካፒታል ገበያ ቅርብ ስለሆኑ የመጀመርያዎቹ ኢንቨስተሮች ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችም አክሲዮን መግዛት ይችላሉ፤›› ሲሉ የሙዓለ ንዋይ ገበያው ምሥረታ ሒደት አስተባባሪ ኃላፊ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የግልና የመንግሥት ጡረታ ተቋማት በቀዳሚነት ኢንቨስት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ 26 አትራፊ የሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ 250 ሚሊዮን ብር የመንግሥትን ድርሻ ያዋጣሉ ተብሏል፡፡ የተቀሩት ደግሞ ሙዓለ ንዋይ ገበያው ሲቋቋም አክሲዮኖቻቸው ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በቅርቡ በኬንያ፣ በእንግሊዝ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በሌሎች አገሮች የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚጀመር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሙዓለ ንዋይ ገበያ ማለት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች (Securities) ወይም አክሲዮኖች የሚገዙበትና የሚሸጡበት በቴክኖሎጂ የታገዘ ገበያ ነው፡፡

ነባር ባለአክሲዮኖች አክሲዮን የሚሻሻጡበት፣ እንዲሁም አዲስ ድርጅት የማቋቋም ሐሳብ ያላቸው ገንዘብ የሚያሰባስቡበት ገበያ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዕዳ ገበያን ጨምሮ ብዙ ተግባራት ይኖሩታል ተብሎ በአዋጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡(ሪፖርተር)

– በቴሌግራም :- https://t.me/etstocks
– በፌስቡክ ፡- https://fb.me/etstocks

ይቀላቀሉና ቤተሰብ ይሁኑን እናመሰግናለን

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top