የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤት ሽያጭ በካሬ ሜትር ቁርጥ ተመን አወጣ

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤት ሽያጭ በካሬ ሜትር ቁርጥ ተመን አወጣ

.በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከተማው የሚያመነጨውን ገቢ ሙሉ በሙሉ አሟጦ ለመሠብሰብ የቆረጠ መስሏል።

አስተዳደሩ በቅርቡ ካካሄደው የቤት ግብር ማሻሻያ በተጨማሪ – በጥልቀት በመግባት ከቤት ሽያጭም የተሻለ ገቢ መሠብሰብ የሚያስችል ኮምጠጥ ያለ ውሳኔ አሳልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀንዓ ያደታ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓም ለከተማው ፋይናንስ ቢሮ በፃፉት ደብዳቤ ፣ በቤት ግብይት ላይ በወቅታዊ የገበያ ዋጋ መሠረት የካፒታል ጌን ፣ የቴምብር ቀረጥ ፣ አሹራ ክፍያ ለማስከፈል የሚያስችል ጥናት መካሄዱን ገልፀው ፤ ቢሮው አዲሱን ቀመር እንዲያፀድቅላቸው ጠይቀዋል ።

ሰሞኑን ፋይናንስ ቢሮ የቀረበለትን አዲስ ቀመር በመቀበሉ የመሬት ስሪት መስሪያ ቤት ባለሙያዎች አዲሱን ቀመር ተግባራዊ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን የወዝ ኒውስ መረጃዎች ጠቁመዋል።

የውሳኔው ማጠንጠኛ በቤት ግብይት ወቅት ዕውነታው እና የሚቀርበው የሽያጭ ውል እጅግ የተራራቀ በመሆኑ – በውሉ ላይ ተመስርቶ የሚገኘው ካፒታል ጌን 15 % ፣ቫት 15% ፣ የቴምብር ቀረጥ 2 % ፣ አሹራ 4% ፣ እንደየ ገቢው ሁኔታ ከ10- 35 % ትርፍ ግብር በተሰኙ የገቢ አርዕስቶች ላይ የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች አየተደረደሩ ሽያጭ ገቢ እንዲደበቅ ተደርጓል የሚል ነው።

በቤት ግብይት ዙሪያ አሳንሶ መዋዋል ፣ አሳንሶ መገመት ፣የስም ዝውውር ማዘግየት ፣ ቤቱ በርካታ ጊዜ ግብይት ቢፈፀምበትም በመንደር ውል እየተዋዋሉ ስም ዝውውር አገልግሎት ሳይጠይቁ ግብይቱን አለማሳወቅ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸው ተመልክቷል።

ይህ የተበላሸ አሰራር የከተማውን የመሬት ስሪት ባለሙያዎች ሲያሳስብ የቆየ ችግር ቢሆንም – ዘግይቶም ቢሆን የከንቲባ አዳነች ካቢኔ ችግሩን ለመፍታት ውሳኔ አሳልፏል ።

የከተማው አስተዳደር አሰራሩን በማስተካከል – ዕውነተኛው የሽያጭ ፍሬ ገንዘብ ላይ ያደርሰኛል በማለት እንደየ ቦታው ደረጃ – አንድ ይዞታ በካሬ ሜትር ሊሸጥ የሚችልበትን ዋጋ ወስኗል።

በአዲሱ ቀመር ቤት ሻጭ እና ገዥ የሚያቀርቡት ውል ላይ የጠቀሱት ገንዘብ ከተቀመጠው የካሬ ሜትር ዋጋ ከበለጠ ተቀባይነት የሚያገኝ ሲሆን ካነሰ ደግሞ አስተዳደሩ ባቀረበው የካሬ ሜትር ዋጋ ብቻ ይስተናገዳል።

የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን በቦታው ስፋት በማባዛት የሚገኘው ውጤት ከሽያጭ ውሉ ጋር በማነፃፀር ብልጫ ባለው ዋጋ ስመ – ንብረት ዝውውሩ ተፈፃሚ እንዲሆን ዶ/ር ቀንዓ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

WZ news / ወዝ ኒውስ
ውድነህ ዘነበ

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top